በመጽሐፉ ውስጥ ክፋትና በጎነት፣ ፍቅርና እምነት፣ ቅንዓትና እርጋታ፣ ጽናትና ፈተና ሰይፍ ጨብጠው በገሃድ ሲሞሻለቁ በምናብ ዓይናችን በሚገባ እናስተውላለን፡፡ በተለየ ሁኔታ ግን የመጻሕፍቱ ገፀ ባሕርያት ከንባባችን በኋላም ቢሆን አብረው የመሰንበት ከፍተኛ ጉልበት አላቸው፡፡ እንዲያውም ልክ እንደ ቅርብ ወዳጆችና ተጎራባቾች አብረውን ያሉ እስከሚመስሉ ድረስ ቤተኛ እስከ መሆን ይደርሳሉ፡፡